ዘረኛ ማን ነው?

Note: This observation was posted on Facebook page of Solomon Seyoum.

ዘረኛ ማን ነው?

ዘረኝነትስ ምንድነው?

————

ዛሬ አርብ በጠዋቱ ወደቢሮዬ አመራሁ፤ የጠበቀኝ እንግዳ ስለህፃናት አመጋገብ የሚያወራ ሰነድ ይዟል፤ ስለልጅ አስተዳደግ (cognitive development) እያወራን ነው፤ ወንድሜ አዲስ አበባ እየኖረ ልጁ በአፋን ኦሮሞ አፏን እንደፈታች ነገርኩት፤ የባህል ቡድኔን ጠይቆ “እናንተማ ዘረኞች ናችሁ” ብሎኝ አረፈው፤ ሳብሰለስል ውዬ ቤቴ ስደርስ ቀጣዩን አስፍሬአለሁ፡፡

ጠለቅ ያለ አካዳሚያዊ ተዋስኦ፣ ኃልዮት፣ ፍፁም ምክንያታዊ ድምዳሜዎች እና ፍፁማዊ አብነቶች የሚጠብቅ አያንብበው፤ አላማዬ በዚህ የግል መብሰልሰል መነሻነት በሚነሱ ውይይቶች እኔም ሆንኩ ሌላ እንዲማርበት ነው፤ በዋለልኝ መኮንን ማሳሰቢያ ልዝጋ፤ ከዚህ አውድ ውጪ አይወሰድ፡፡

ወደ ጉዳዬ ስገባ በቅድሚያ እንደኔው አይነቱ ፈንዲሻ ምሁር እና ልሂቅ የደባለቀውን ‹ዘረኝነት› እና የባህል ቡድን ወገንተኝነት ይለይ፡፡ በርግጥ ለዚህ መምታታት ዋነኛው ተጠያቂ ‹ዘረኝነት ተዋጊው ‹ዘረኛ› ልሂቅ ነው፡፡

የስነ ሰብዕ ምሁራን “ዘር” ብሎ ልዩነት መጥቀስ፣ የሚመች ስህተት ሆኖ (a convenient inaccuracy) እንጂ በሰው መካከል የዘር ልዩነት እንደሌለ ይስማማሉ፤ ሊኖር ቢችል እንኳ፣ በአከባቢያዊ ልዩነት የሚከሰት የ gene-pool ቁጥር ልዩነት ብቻ ነው፤ እሱም የዘር ልዩነት ሆኖ እርስበርስ መዳቀልን (መራባትን) አይከለክልም፡፡

ታዲያ ‹ዘረኝነት› ተዋጊው አግላይ (‹የአንድነት› ኃይል by default) ስለየትኛው የዘር ልዩነት (ዘረኝነት) እያወራ ነው?

የመጀመሪያው ስለ ዝምድና ‹ዘረኝነት› ይመስላል፤ የዘርፉ ምሁራን “integral nationalism” ወይም የስጋ/የደም ትስስር ቅድምና የሚሉት፤ በባህል ቡድኔ ጉዳዩ በዋናነት ዝምድና መቁጠር እንጂ ‹የአንድነት› ኃይሉ ጠርዝ ድረስ ወስዶ የሚያራግበውን የ‹ዘረኝነት› እሳቤ አይወክልም፤ ለምሳሌ ኦሮሞ ጎሳ የሚለው ቡድን የመጨረሻው ክፍል እርስ በርሱ አይጋባም፤ ዘመናዊ የቤተሰብ ህግም በስጋ ዘመዳማቾች መካከል (እስከተወሰነ ቤት) በስነህይወታዊ እና ባህላዊ ምክንያቶች የተነሳ የርስ በርስ ሩካቤ ስጋና ጋብቻ ይከለከላል፡፡ ኦሮሞ ዘመናዊ ህግ ባልነበረበት ይህንኑ ክልከላ አስተማማኝ ለማድረግ ነው ቡድኑን የለየው፡፡

ነገር ግን ስለብዝሃ ብሔር/ባህል ስታወራ፣ ‹የአንድነት› ኃይሉ ስነ-ህይወታዊ ዘረኝነት አድርጎ ይወስዳል፤ አንዴ ገረሱ ቱፋና አቤኔዘር ስለዚሁ ጉዳይ በኢሳት ቴሌቭዥን ተወያዩ፤ አንዱ ‹የአንድነት› ኃይል ቀጣዩን ጋዜጣ ላይ አወጣ፡-

“በኢትዮጵያ ኦሮሞ ወይም አማራ የሚባል ንፁህ ዘር የለም፤ ኦሮሞ አፍ መፍቻ ቋንቋው ኦሮምኛ [“አፋን ኦሮሞ” ለማለት ነው] የሆነ ማህበረሰብ ነው፤ አማራም አፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ የሆነ ማህበረሰብ ነው፤ አማራ የሚባል ንፁህ ዘር የለም፤ አማራ የአገው፣ የቤጃ፣ የኩናማ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ … ክልስ ዝርያ ነው፤ … በተመሳሳይ ኦሮሞም የደቡብ ነገዶችና የአማራ ክልስ ዘር ነው፤ እንደ አማራ ክልስ ዘር ነው”

እናንተ “ዘረ-እኛዎች” !! የሰው ዘር ሰው ነው፤ በሰው መካከል ዘረኝነት የለም፤ ስሙ፡፡

ሁለተኛው ስህተት የባህል ቡድን ወገናዊነት እንደ ‹ዘረኝነት› መውሰዱ ነው፤ ‹የአንድነት› አቀንቃኝ ነኝ ለሚለው ወገን ኢትዮጵያዊነት ማቀንቀን የባህል ቡድን ወገናዊነት (በሱ ቋንቋ ዘረኝነት) አይመስለውም፤ እንኳን የሱ አይነት “አንዱን ጥሎ አንዱን አንተልጥሎ” አይነቱ ቀርቶ፣ እውነተኛ አንድነት እንኳ ቢሆን ማለቴ ነው፡፡ የወገንክለትን ባሳፋህ ቁጥር ከወገናዊነት ነፃ አትሆንም፤ አለም ብታዳርስ ፅረአርያሙ ይቀረሃል፡፡

ዞሮ ዞሮ የባህል ቡድን ወገናዊነት ከቤተሰብ ጀምሮ የሚሰፋ ነው፤ ለምሳሌ ቀጣዩ ጥቅስ የማን እንደሆነ ሳያውቅ ያነበበ ‹ያንድነት› አቀንቃኝ ካወቀ በኋላ ስለዘርኝነቱ/ጥበቱ ያሳደረው ስሜት እንደሚቀየርበት እገምታለሁ፡፡ እነሆ፡-

“————— በ————- ቤት ተከብሮ፣ ተቆላምጦ ተከብቦ አደገ፡፡ ነገር ግን ያ ሁሉ መንከብከብ፣ ያ ሁሉ መቆላመጥ ምን ሲሆን ተልብ ሊደርስ ነው፤ ነፍስ እያወቀ፣ አዕምሮ እያወጣ ሄደ፤ ልዥነቱ ቀረ፡፡ ያገሩ ነፋስ፣ ያገሩ ወንዝ ይናፍቀው ገባ፤ ድሮ ይሮጥበት የነበረ መስክ፣ ይድህበት የነበረ እልፍኝ፣ ውል ይለው ይናፍቀው ጀመር፡፡”

ያንድነት ኃይሎች! ይህ ቀየ/መንደር መናፈቅ ጥበት ነው ሰውነት? ጥበት ከሆነ ይህ ጠባብ ማን ነው?

.

.

.

.

.

 

እንዲህ የተባለለት ዳግማዊ አጤ ምንሊክ ነው፡፡ (አፈወርቅ ገብረየሱስ፤ አጤ ምንሊክ ገፅ 15)

ለመሆኑ፣

1. መቅደላ ሀገሩ አይደለም እንዴ?

2. መቅደላ ነፋስ የለም እንዴ?

3. መቅደላ ወንዝ የለም እንዴ?

ነገሩ ወዲህ ነው፤ ታዋቂዋ አፍሪካ-አሜሪካዊት የስነ-ሰብዕ ተመራማሪ ቶኒ ሞርሰን፣ “ትውስታ (Memory) ልክ እንደ ውሃ ነው፤ ሁልጊዜ ወደ ምንጩ ለመመለስ ይጥራል” ያለችው ነው የሚገዛው፤ ምንሊክ መናፈቁ ሰው በመሆኑ እንጂ አህያ ቢሆን ወዲያው በረሳው፤ ጠባብነት/ዘረኝነት ሌላ ነው፡፡

መስፍን ወልደ ማርያም “አውቆ አበድ” ይመስለኛል፤ አዳፍኔ ገፅ 27 ላይ አዳፍኔን ሲፅፍ ከኢትዮጵያዊ ማንነቱ— “ከኢትዮጵያዊ ትውልዴ፣ ከኢትዮጵያዊ አስተዳደጌና ስሜቴ፣ ከበርበሬው መፋጀት እና ከቡናው ትኩስነት ራሴን ሙሉ በሙሉ አግልዬ ስለኢትዮጵያ መናገር እችላለሁ ብዬ አልዋሽም፡፡” ይላል፡፡

ታዲያ ምኑ ነው “አውቆ አበድ” የሚል ዘለፋ ጋር ያደረሰህ አትሉም? ቀጣዩ ድንቅ የመስፍን ማስገንዘቢያም አይደለም፤ መስፍን “በኔ ውስጥ የሰረፀው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በምድረ ኢትዮጵያ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ሁሉ የሰረፀ ነው በማለትም ራሴን አልለጥጥም፤ እኔ ባለፍሁበት የቤተሰብና የጎረቤት ተፅዕኖ በምድረ ኢትዮጵያ ያሉ ሰዎች ሁሉ አልፈዋል አልልም፡፡” ይላል፡፡

መቼም ፕሮፍ በዚህ ሀሳቡ እጅግ አስደስቶኛል፤ ቀጥሎ ስለትምህርት ቤት ህይወቱ ያለው ደግሞ የባሰ አስደማሚ ነው፤

“… ትምህርት ቤት ባሳለፍኋቸው አመታት ከመላ ኢትዮጵያ ከመጡ ጓደኞች ጋር አድጌአለሁ፤ የብዙ ኢትዮጵውያን ጎሳዎች ዘፈኖች ደስ እያለኝ ጨፍሬአለሁ፤ … ደስ እያለኝ …፡፡ እነዚህ ዘፈኖች እና ጭፈራዎች ሁሉ በኢትዮጵያውነት የኔ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡”

መቼም ግሩም ነው፡፡ የመስፍን ችግር እንዲህ አስውቦ የጨረሰውን ጉዳይ ትቶ ወረድ ሲል በጅምላ በጎሰኝነት፣ በዘረኝነት፣ በጠባብነት መንቀፉ ነው፤ በመክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፣ በአዳፍኔ እና በሰሞነኛው ዘጭ እንበጭም በአዕምሮው ያለችው ኢትዮጵያ ያቺው በ “Greater Tradition” ተረት ያታጀለችው ከአንኮበር ወደሰሜን ያለችዋ ናት፡፡ ከዚህ ውጪ ከሆንክ ዘረኛ፣ ጎሰኛ፣ ጠባብ ነህ፡፡

***

የኦሮሞን አብነት ብንወስድ ‹የአንድነት› ኃይሉ እንደሚለው ‹ዘረኛ› ሳይሆን የባህል ወጋኝ እንደሆነ መረዳት አይከብድም፤ ለምን ያልን እንደሆን ለምሳሌ ፖል ባክስተር “A number of ethnographers have attested to the fact that Oromo share core common cultural values and modes of thought.” ይላል፡፡ (Baxter 1985: 1994: 284)

ሁልቲን በበኩሉ ሲያጠናክር “the people are not racial group on the basis of shared physical characteristics. Oromo could be termed a cultural category” ይላል፡፡ (Hultin 1987:2)

ፖል ባክስተር “በክብር በተጋበዝኩባቸው የኦሮሞ አውደ ጥናቶች በርሊን፣ አምስተርዳም፣ ሎንዶን፣ ሜልቦርን፣ ቶሮንቶ – የኦሮሞ ባህል ብያኔና ክብር ዋናው ጉዳይ ነበር፡፡ ለየትኛውም የተጨቆኑ ብሔረሰቦች እንደሆነው ሁሉ፣ በኦሮሞ ምሁራን ዘንድም ቋንቋና ሀገረ-ሰባዊ ባህል (folk culture) የማንነት ትዕምርት ናቸው” ሲል ፅፏል (Baxter 1994 :171)::

ነገር ግን ኦሮሞ ከሌላው ባህል አንጻርስ ምን አቋም አለው? ታላቁ የኦሮሞ ባህል፣ እሴት፣ እና ማንነት ተመራማሪ፣ ኤርትራዊው ፕሮፌስር አስመሮም ለገሰ “Oromo democracy” በተባለ ጥናቱ ያለውን እናስፍር፡-

“በኦሮሞ ታሪክ ውስጥ ወረራ (Conquest) በወራሪ እና ተወራሪ መካከል ይህ ነው የሚባል ማህበራዊ ልዩነት ከቶ አላመጣም፡፡ ተወራሪዎቹ፣ የነዋሪነት ሙሉ መብትና ግዴታ ይጎናፀፋሉ፣ ያልተሸራረፈ መብትና ግዴታ፡፡ ሁለቱን አካላት እንደ ወራሪና ተወራሪ ማየት የቦረናን የእኩልነት መርህ የሚጥስ ነው፡፡”

(1989፡17)፡፡

ታዲያ ‹የአንድነት› ኃይሉ የሚፈልገው (በርግጥ በተግባር አይደለም) አንድነት እንዲመጣ የሚረዳው የታጋሪዮሾች መስፋት ያልመጣ በምን ምክንያት ነው?

የዚህን መልስ ለማግኘት አቋራጩ ራሱን ‹የአንድነት› አቀንቃኙን መፈተሸ ነው፤ አቃፊ ነው አግላይ? ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ፣ እ.ኤ.አ በ1989 ዓ.ም በፃፈው፤ “Red tears: war, famine and revolution in Ethiopia” መፅሐፍ፡-

“እነዚያ ጥቂት ‘ዕድለኛ’ ኦሮሞዎች ወደ ኢትዮጵያ ስርዓት ልብ እና መንፈስ የሚቀላቅላቸውን መስፈርት ይዘዋል፣ አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ በባህል አማራ ከመሆናቸውም በላይ የሚያወሩትም አማርኛ ነበር፡፡ ቀንደኛ የኢትዮጵያዊ (ጠቅላይ) ብሔርተኝነት አቀንቃኞች ነበሩ፤ ለንጉሱም ታማኝ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሆኖም፣ በአማራ ልሂቃን ዘንድ በእኩልነት አይታዩም ነበር፡፡”

ሙኩሪያ ቡልቻ በበኩሉ ስለነዚህ ተለንቃጭ (አስሚላንዶ) ኦሮሞዎች ያለው የአንድነት ኃይሉን ‹ዘረኝነት›/አግላይነት ይመሰክራል፡-

“The life of assimilated Oromos was often peripheral. In spite of their total submission to “pressure for their cultural suicide and to the dominance of the Amhara over non-Amhara peoples in all aspects of life”, they were seldom treated as equals by Amhara. The Amharazation of the Oromo and other groups was attempted “without integrating them as equals or allowing them to share power in any meaningful way” As the “Amhara mask” they wore was often too transparent, assimilated Oromos rarely reached decision-making positions within the Ethiopian bureaucracy.”

ሶስተኛው አጋም ጠቀም ነው፤ ስጋ ዝምድናን እና የባህል ቡድንተኝነትን የሚደባልቅ፡፡

ዩሱፍ ያሲን በ “ኢትዮጵያዊነት… “ መፅሀፉ ያወጋንን ባጭሩ፤ የዛሬው “የኢትዮጵያ አውራ ብሔርተኛ” ተኮላ ሀጎስ (ፕ/ር) ከ41 አመት በፊት በ1969 አንድ ስእል ስሎ ህግ ትምህርት ቤት ለእይታ አቀረበ፤ ተኮላ የስዕሉን ወካይነት በራሱ አስቦ ከስሩ “The Ethiopian” – (ኢትዮጵያዊው) የሚል ፅሁፍ አኑሯል፡፡ ስእሉን ብታዩት ብታዩት አንድ የምታውቁት የሰሜን ሸዋ ጎልማሳ ነው የሚመስለው፡፡ ታዲያ በወቅቱ ለነበረው ተኮላ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህን ሰው ይመስላል፡፡ ታዲያ ይሄን የተረዳ አንድ ተመልካች ተኮላ “The” ያለውን ጅምላ ወካይ በርሳስ ወደ “An”-( ነጠላ) ቀይሮ “An Ethiopian” – “አንድ ኢትዮጵያዊ” አደረገው፡፡ ተኮላ እንደ ዘር ልዩነት የተወሰደውን የቆዳ ቀለም ብዝሀነት እንኳ መዘንጋቱ ነበር፡፡

በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንዱን አልፎ ሂያጅ ‹ሀበሻነቱን/ ኢትዮጵያዊነቱን› በመልኩ አውቀው እንዳናገሩት መስማት የተለመደ ነው፡፡ እውነቱ ግን ይህ ሰው ወይ ኦሮሞ ወይ አማራ ወይ ትግሬ ወይ …. እንጂ በእነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያውነት ትርጉም ውስጥ የተረሱትን አኙዋክ ጉሙዝ፣ በርታ፣ ኑዌር … አይሆንም

አሊያም በመልኩ መምሰል ኢትዮጵያነቱን ቢያውቅ እንኳ “ወለኔ ነኝ” “ባህረ ወርቅ ነኝ” ብሎ የባህል ቡድኑን ቢነግረው ያለማወቅ እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ታዲያ ይሄ ነው ኢትጵዊነት?

ጌታቸው ኃይሌ በ “አንዳፍታ ላውጋችሁ” ላይ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ነግሮ አንዲት ሴራሊዮናዊት በቤት ውስጥ ስራ እንድትረዳው ለመቅጠር ቢያናግራት፣ “ደግሞ እናንተ ጋ፤ በዲፕሎማት ቤት አገልጋይነት መጥቼ ኖሬ አይቻለሁ፤ ዘረኝነታችሁ ከልክ ያለፈ ነው፤ በቆዳ ቀለሜ የተነሳ ያየሁትን አበሳ እያወቅሁ ደግሜ አንተ ጋ፤ ወግድ!” (ቃል በቃል አይደለም) እንዳለችው ተርኳል፡፡

ኢትዮጵያዊ/ት ጥቁር የለም/ የለችም? ‹ዘረኝነት› ተዋጊዎቹ ጥበታቸው እዚህ ጋ ነው፤ ኢትዮጵያዊ/ት ሁሉ የሸዋ ሰው ይመስላል፤ ትመስላለች፡፡

እነሆ ሌላ ወግ፤ አንድ ጥቁር ሰው ወደ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቢሮ ሄደ፤ ከአስተናጋጁ ጋር በእንግሊዘኛ እያወሩ በመሀል “by the way, why do you prefer Gambella (Ethiopia) to your home West Africa?” ሲል የቢሮው ሰራተኛ ይጠይቀዋል፡፡ ተስተናጋጁ ደነገጠ፤ ምንም አልመለሰምም፡፡

ይህ ሰው የነፃነት፣ የእኩልነት እና የሰብአዊ መብት አርበኛው፣ ኢትዮጵያዊው ኦባንግ ሚቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የ ‹አንድነት› ኃይሉ የ‹ኢትዮጵያዊ ምስል› በውስን የቆዳ ቀለም፣ በውስን ቋንቋ (አማርኛ ብቻ ማለት ይቻላል)፣ እና በተለመዱ ምንችክ ባህሎች ላይ የተንጠለጠለ ግን ይህ መሆኑን የማያውቀው ጠባብ ድንቁርና ነው፡፡

በሀይማኖታዊ ማንነት በኩልም ሰላም የመሰለው ‹አናሳው› ስላጎነበሰ እንጂ የልዩነት እውቀትና አክብሮት ሰፍኖ አይደለም፡፡ የወሎው መሀመድ አሊ በጫና ብዛት ክርስትና ሊነሱ ሲሉ አዝማሪው፣

“ የየጁ ነጋዴ ሀር አምጣ ሀር አምጣ

የተንታ ነጋዴ ሀር አምጣ ሀር አምጣ

እንዲህ ያለ አንገት እንዴት ማተብ ይጣ፡፡” ብሎ ነበር፡፡

‹የአንድነት› ኃይሉ መቼም ይሄ “ብሉያዊ ነው፤ ዘመናችንን አይገልፅም” ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡

“እስላም ክርስቲያኑን ባንድነት ያዋሃደው

ማተቡ ነው ድሮም አብሮ የገመደው”

ይህ ስንኝ የትዝታ ንግስት ከምንላት የክፍለ ዘመናችን አንጎራጓሪ ቤዛወርቅ አስፈው ዘፈን የተገኘ ነው፤ ትርጉም ይሰጣል? እስቲ ፍረዱ! ማን ልፅፈው ይችላል? ስሙ ሳይሆን አስተሳሰቡ፤ ‹የአንድነት› አቀንቃኝ መሆኑ አያጠራጥርም፤ ነገር ግን በተሳሳተ መንገድ፤ ወዳጄ ዳዊት ሰለሞን “ክትፎን በፖፖ” የሚላት አይነት፡፡

ልህቁ፣ በተለይ የአንድነቱ አቀንቃኝ፣ ከተሳሳተ መነሻ በመነሳቱ ትክክለኛ ድምዳሜ አንጠብቅበትም፤ እነዚህ አግላይ ኢትዮጵያዊነት አቀንቃኞች፤ (Sorenson “Abyssinian Fundamentalist” ተስፋዬ “ኢትዮ-አማሮች” ይሏቸዋል) በሽታቸውን አያውቁም፤

በርግጥ ‹በአንድነት› ኃይሉ ውስጥ ከባህል ቡድን ማን ይበዛል?

“ዘረ እኛዎች” አለ በፍቃዱ ሞረዳ፡፡
የምንፀየፈውን አንኑር!

Leave a Comment